ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቀውስ በኦሮሚያ ክልል በተባባሰው ፖለቲካዊ እና ብሔር ተኮር ውጥረት ሳቢያ እጅጉን ተባብሷል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከዚህ ቀደም ሊደርስባቸው ወዳልቻላቸው ከተሞች እየቀረበ ጥቃት እየፈጸመ ነው። አዳዲስ ምልምሎችን አሰልጥነው የምርቃት ሥነ ሥርዓት በከተሞቹ ያካሂዳሉ።
ቀውሱን ለመግታት ከቡድኑ ጋር ንግግር የማድረግ ሐሳብን ገሸሽ ያደረገው መንግሥት፣ ምላሽ እየሰጠ ያለው ወታደሮች በማሠማራት እና የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት በማካሄድ ነው።
ነገሩን የበለጠ ያባባሰው ደግሞ የአማራ ሚሊሻዎች ወደ ኦሮሚያ እየገቡ ከታጣቂዎቹ ጋር እየተዋጊ ነው መባሉ ነው።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ራሱን እንደ ኦሮሞ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ ሲገልጽ፣ ከተቃዋሚዎች ጋር ትስስር ባላቸው መገናኛ ብዙኃን ዕውቅና ተሰጥቶታል። ከዓመታት በፊት ግን ቡድኑ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ የተገለለ ነበር።
መንግሥት ያዋቀረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንደሚለው በኦሮሚያ ባለፉት አምስት ወራት “በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዘግናኝ ሁኔታ ተገድለዋል።”
የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ በኅዳር ወር የተፈናቀሉ ሰዎች ከ700 ሺህ ሲበልጡ፣ በታኅሣሥ መባቻ ተጨማሪ 220 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል መገደዳቸውን ገልጿል።
በግጭቱ ታሳታፊ የሆኑት ሁሉም ቡድኖች የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን አያምኑም።
መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ ለምን የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ አዳገተው?
ሰብአዊ ቀውስ በሚባባስባቸው አገራት ዝርዝር ኢትዮጵያ ሁለተኛ ተባለች
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ሸኔ የፈጸማቸው ጥቃቶች ምን ያመለክታሉ?
ኅዳር ላይ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እየጠነከረ መምጣቱን በሚጠቁም ሁኔታ ተዋጊዎቹ ነቀምቴ ገብተው ነበር። ነቀምቴ ስትራቴጂካዊ ከተማ ከመሆኗ ባሻገር መስመሩ ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ፣ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትውልድ ቀዬ እንዲሁም ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ወደሚገነባበት ስፍራ ይወስዳል።
ነቀምቴ ስለደረሰው ጥቃት መንግሥት አስተያየት አልሰጠም። መንግሥት ለሌሎች ጥቃቶችን በተመለከተም አስተያየት ሲሰጥ አይስተዋል።
ታጣቂዎቹ በነቀምቴ “የፖለቲከ እስረኞችን” ነጻ ማውጣታቸውን ሲናገሩ ነበር።
ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በታጣቂዎች እና በመንግሥት ሠራዊት የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ የንጹሃን ሕይወት ተቀጥፏል።
በጥቃቱ የ27 ዓመት ወንድ ልጁን እና የ16 ዓመት ሴት ልጁን እንዳጣ አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጿል።
የመንግሥት ወታደሮች ወደ ቤቱ እንደተኮሱ የሚናገረው ነዋሪው “ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ ነበር ከእንቅልፋችን የተነሳነው። ውጪ ተኩስ ይሰማ ስለነበር ሳንሄድ ቀረን። ሁለቱም ልጆቼ ቤት ውስጥ ሳሉ” ተገደሉ ብሏል።
‘አንዳችም የሰውነት ክፍል አልተገኘም’
የሌሎች ከተሞች ነዋሪዎችም ስለ ግጭቱ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
በጎሮ ከተማ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በመንግሥት ወታደሮች ላይ የበላይነት ካገኙ በኋላ፣ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ወጣት ወንዶች የቆሰሉ ታጣቂዎችን ተሸክሞ ለማጓጓዝ እንዲያግዙ ሲያስገድዱ እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ወጣቶቹ ይህን ሲፈጽሙ በድሮን ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። በዚህም ወጣቶቹ እና የተወሰኑ ታጣቂዎች ተገድለዋል።
ክስተቱን በሐዘን በተሰበረ ድምጽ የገለጸ አንድ ነዋሪ ሦስት ተማሪ ወንድሞቹ እንደተገደሉበት ተናግሯል።
“ወንድሞቼን አልቀርኳቸውም። አንዳችም እንኳን የሰውነት ክፍላቸው አልተገኘም” ብሏል።
የድሮን ጥቃቶቹ፣ መንግሥት በትግራይ እንዳደረገው ሁሉ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትንም ለመግታት ተመሳሳይ ወታደራዊ ስትራቴጂ እየተጠቀ ነው የሚል ፍርሀት አጭሯል።
የአፍሪካ ኅብረት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ማስፈረሙ አይዘነጋም።
የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የኢትዮጵያ ተንታኝ ዊልያም ዴቪሰን “በትግራይ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን ቢጎዱም ዒላማው ከፍተኛ ወታደራዎ ተሽከርካሪዎች እና መሣሪያዎች ናቸው። በኦሮሚያ ግን የድሮን ጥቃት የተሰነዘሩት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወታደሮች የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው። ከተሞች በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ሲውሉ ድጋፍ ያሳዩ ሰዎችን ለመቅጣትም፣ ከተሞች በታጣቂዎች ከተያዙ በኋላ የድሮን ጥቃቶች ተሰንዝረዋል” ይላል።
በኅዳር ወር በጮቢ ወረዳ “የምርቃት ሥነ ሥርዓት” ላይ የአየር ድብደባ ተፈጽሟል። ነዋሪዎቹ ይህንን ሥነ ሥርዓት የታደሙት ወደውና ፈቅደው እንዳልነበረ አንድ የዐይን እማኝ ከአሶሺየትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
“ታጣቂዎቹ ነዋሪዎች ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ ስለተናገሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል። ጥቃቱ ከደረሰ ከ20 ደቂቃ በኋላ ያየሁት አሰቃቂ ነው። ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አዛውንቶች እና የተወሰኑ ታጣቂዎች ተገድለዋል” ብለዋል።
በጥቅምት ወር በርካታ የአየር ጥቃቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰው በቢላ ከተማ የደረሰው ጥቃት ነው።
በገበያ ቀን በከተማዋ ማዕከል በተፈጸመው ጥቃት ሳቢያ ከ80 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የእህታቸውን ልጅ ጨምሮ 11 ሰዎች እንደቀበሩ አንድ ቄስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ያጣሁት የእህቴ ልጅ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበር። ሦስት ቤቶች ውስጥ በእያንዳንዳቸው ሁለት ሰዎች ሞተዋል” ብለዋል።
ወታደሮች ነዋሪዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ደጋፊ ናቸው በሚል ጥርጣሬ እንደሚተኩሱባቸው ተገልጿል። ከዚያም አስክሬናቸውን ቤተሰብ እንዳይወስድ ይከለክላሉ።
በተለይም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን የተቀላቀለ ቤተሰብ ያላቸው ሰዎችን ዘለግ ላለ ጊዜ በማገት ያለ ፍርድ እንደሚያቆዩም ይከሰሳሉ።
እገታ
መቀመጫቸውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉት ተንታኝ መብራቱ ከለቻ እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን የመጡበት የኦሮሞ ሕዝብ ድጋፍ አሁን እየታየ ባለው ነውጥ ሳቢያ ሊቀለበስ ይችላል።
“የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ይህንን ፕሮፓጋንዳ ተዋጊዎችን ለመመልመል ሊያወለው ይችላል። የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት የተመናመነውን [እንደ ምግብ ያሉ] የመሠረታዊ አገልግሎት አቅርቦቶቹን ለማሟላት ሊያውለው ይችላል” ሲሉ ያስረዳሉ።
በምዕራብ ኦሮሚያ ጫካ የሽምቅ ውጊያ የሚያካሂደው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኢትዮጵያ ያለውን ማኅበረሰባዊ የመሬት እና የሥልጣን ሽኩቻ ያንጸባርቃል።
ሁሉም ማኅበረሰብ በማንነቱ በመኩራት ለባህሉ እና ለቋንቋው ዕውቅና እና ክብር ሲሰጥ ይስተዋላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ማንነት በመገንባት የፖለቲካ ፓርቲዎች የብሔር ውግንናቸውን እንዲተዉ ለማድረግ ቢሞክሩም ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “ኦሮሚያ ራስ ገዝ” ትሁን የሚል አቋም ያራምዳል።
ይህ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ ባይታወቅም፣ የቡድኑ ተቺዎች ኦሮሚያ እንድትገነጠል ይፈልጋሉ ብለው ይሰጋሉ።
የሥራ አጥ ቁጥር ከመጨመሩ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመታፈናቸው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮምኛ ቀንቋን ከአማርኛ ጎን ለጎን የሥራ ቋንቋ ለማድረግ ካለመቻላቸው ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን የመደገፍ አዝማሚያ ይስተዋላል።
ዊልያም ዴቪሰን በበኩሉ፣ ቡድኑ የአሁን ካለው አቅም በላይ በተጋነነ ሁኔታ እንዳይታይ ያስጠነቅቃል።
“ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚንቀሳቀስባቸውን ቦታዎች አስፍቷል፣ የተዋጊዎቹንም ቁጥር ጨምሯል። ይህም መንግሥት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ባፈነበት ወቅት ነው። ሆኖም ግን እንኳን ለፌደራል መንግሥቱ ለክልሉም መንግሥት ስጋት ለመሆን አልደረሰም” ይላል።
ቡድኑ ምን ያህል ተዋጊዎች ቡድኑ እንዳለው ግልጽ አይደለም። መብራቱ እንደሚሉት “ፈጣን እና መጠኑ የተገደበ ጥቃት በመፈጸም የመንግሥትን አቅም ለማዳከም የሚደረገው ጥረት” የቡድኑ ተዋጊዎች ያን ያህል የተጋነነ ቁጥር አላቸው ለማለት አያስደፍርም።
ቡድኑ ባንክ በመዝረፍ እንዲሁም ነጋዴዎችን፣ ሠራተኞችን እና የመንግሥት አመራሮችን አግቶ ገንዘብ በመጠየቅም ሲከሰስ ቆይቷል።
ከዚህ ቀደም የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች አዳ በርጋ በሚባል አካባቢ ታግተው እንደነበር አይዘነጋም። የታገቱትን 17 ሠራተኞች ለማስለቀቅ ከ300,000 እስከ 500,000 ብር ገደማ መከፈሉን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የሚሊሻ ውጊያ
ነገሩን የበለጠ አስከፊ የሚያደረገው ታጣቂ ቡድኑ በብዛት አርሶ አደር የሆኑ የአማራ ተወላጅ ንጹሃንን በመግደል መከሰሱ ነው።
እነዚህን ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል ሊያስወጣቸው ይፈልጋል የሚል ፍርሃት ከመንገሡም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩት ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ ለመኖር ተገደዋል።
ፋኖ የሚባለው የአማራ ሚሊሻ ወደ ኦሮሚያ ክልል ገብቶ የአማራ ተወላጆችን ለመከላከል እየሞከረ እንደሆነ ይነገራል።
እነሱም ተመሳሳይ ክስ የሚቀርብባቸው ሲሆን፣ በምዕራብ ኦሮሚያ አምስት ወረዳዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ተከሰዋል።
አንድ የኦሮሚያ ባለሥልጣን እንዳሉት፣ በኪራሙ ወረዳ ብቻ ሚሊሻዎች 244 ንጹሃን ኦሮሞዎችን ሲገድሉ፣ 568 ቤቶች ተቃጥለዋል፣ 25 ሺህ ከብቶችም ተዘርፈዋል።
በኅዳር፣ አንጋር ጉቴ በተባለ ከተማ ስምንት ቤተሶቹን እንዳጣ የተናገረው ታዋቂው ምሑር ሐሰን ዩሱፍ ነው።
ዳኞች እና የመንግሥት ሠራተኞችም በሚሊሻዎቹ እንደተገደሉ የሚጠቁሙ ሌሎች ሪፖርቶች ወጥተዋል።
ባለፈው ነሐሴ በአሙሩ ወረዳ 60 ንጹሃን ዜጎች ከአማራ ክልል የመጡትን ጨምሮ በታጣቂዎች መገደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል። የፋኖ አባላት ስለመሆናቸው ያለው ነገር ግን የለም።
“ከተፈናቀሉት መካከል ነፍሰ ጡር ሴቶች እና በቅርብ የወለዱ እናቶች ይገኙበታል” ሲሉ ኪረሙ ወረዳ የሚኖሩ አንድ የኦሮሞ አዛውንት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች፣ የፋኖ ታጣቂዎች ግዛት የማስፋፋት እና የኢትዮጵያን ውስጣዊ ድንበርን የመከለስ ንቅናቄ ላይ እንደሆኑ ያምናሉ።
በትግራይ ክልል ከትግራይ ኃይሎች ጋር በተደረገው ውጊያ የተሳተፉት እነዚህ ሚሊሻዎች በምዕራብ ትግራይ ለም የእርሻ መሬት ለማስፋፋት ውጊያውን እንደተጠቀሙ እና ተመሳሳይ ነገር በኦሮሚያ ሊከሰት ይችላል ብለው የሚሰጉ አሉ።
ሆኖም ግን ፋኖ ወደ ኦሮሚያ መግባቱን የማያምኑት የአማራ ተወላጆች እንደሚሉት ከሆነ፣ ለአራት ዓመታት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከደረሰ ጥቃት በኋላ እራሳቸውን እንዲከላከሉ በኦሮሚያ ክልል የሚሊሻ ሥልጠና እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚደግፉ የአማራ እንዲሁም የኦሮሞ ተወላጆች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን እና ህወሓትን አያምኑም።
ለዚህም አምና ሁለቱ ቡድኖች በጣምራ ለመሥራት ተስማምተው ሥልጣን ለመጨበጥ ወደ አዲስ አበባ ግስጋሴ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ።
የትግራይ ኃይሎች ከዚያ በኋላ ወደ ትግራይ ተመልሰው ከፌደራሉ ኃይሎች ጋር ከፍተኛ ውጊያ ካደረጉ በኋላ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ተደርጎ ወደ ሰላም ስምምነት መምጣታቸው ይታወሳል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ በኦሮሚያ ድንገተኛ ጥqኣቶች መፈጸሙን ጨምሯል። ጎን ለጎን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም ይገልጻል።
መንግሥት በበኩሉ ንግግር እንደማያደርግ ገልጾ ቡድኑን “ግልጽ አመራር እና ፖለቲካዊ አጀንዳ የሌለው አሸባሪ” ሲል ገልጾታል።
ሆኖም ግን መንግሥት ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና በሚያሳይ መልኩ የኦሮሞ ተወላጅ የምክር ቤት አባላት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ንግግር እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ከእነዚህ አንዱ የሆኑት ብዙአየሁ ደገፋ “በትግራይ የታየው የሰላም ስምምነት በኦሮሚያም መደገም አለበት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኦሮሞ አክቲቪስቶችም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ለተረሳው ጦርነት” ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ከአሥርታት ጭቆና በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ለኢትዮጵያ የሰላምና ዴሞክራሲ ተስፋ ይፈነጥቃል የሚለው ተስፋ እየሳሳ ከመጣ ሰነባብቷል።
በተቃራኒው ውጥረት ነግሷል። የፖለቲካ እና የብሔር ተቀናቃኞች የቀደመ ቁርሾ ለማወራረድ ሲሞክሩ ይታያል። የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት በሚለው ላይም የተለያየ አቋም ነው ያላቸው።
መብራቱ እንደሚሉት፣ ልዩነቶችን ለመፍታት ሁሉም ፓርቲዎች እና ቡድኖች የተሳተፉበት ብሔራዊ ውይይት ያስፈልጋል።
“ከዚህ መልከ ብዙ ግጭትና ነውጥ አገሪቷ እንድትወጣ እውነተኛ እና አካታች የሰላም ሂደት ሊኖር ይገባል። ለግጭቶቹ ሰላማዊ መፍትሄ ካልተገኘ የንጹሃን ጉዳት ይባባሳል። ይህም ለአገሪቷ እና ለቀጠናው ቀውስ ነው” ይላሉ።